ከታሪክ ድርሳናት “የስመ ጥሩዋና የባለውለታዋ ንግሥት የግርማዊት እቴጌ መነን አጭር የህይወት ታሪክ።”

💚💛❤️
ግርማዊት እቴጌ መነን ባ፲፰፻፹፫ ዓመተ ምሕረት መጋቢት ፳፭ ቀን በወሎ ጠቅላይ ግዛት በአምባሰል አውራጃ ልዩ ስሙ “ዕጓ” ከተባለው ቀበሌ ከጃንጥራር አስፋውና ከክብርት ወይዘሮ ስሂን ሚካኤል ተወልደው ደልባ ጊዮርጊስ በሚባለው ቤተ ክርስቲያን የሥላሴን ልጅነት በጥምቀት ተቀበሉ።
ስመ ጥምቀታቸውም ወለተ ጊዮርጊስ ተብሎ ተሰየመ። የዓለም ስማቸው ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ በመጣው በወይዘሮ ስም መነን የሚባለውን ስም ወረሱ።
ግርማዊት እቴጌ መነን የሕጻንነታቸውን ወራት እጅግ በመከባከብና በምቾት ካሳለፉ በኋላ ባ፭ ዓመታቸው እንደ ቀደሙት መሳፍንትና ባላባቶች ልጆች ልማድ በአባትና በእናታቸው ቤት መምህር ተደርጎላቸው የሀገራቸውን ቋንቋ አጥርተው ተምረው ማንበብና መጻፍ አወቁ። የአማርኛ ቋንቋ መምህሮቻቸውም መምህር ማዕዱና አባ ወርቅነህ ይባሉ ነበር።
ከዚህም በቀር ከትምህርት ውጭ በሆነው በትርፍ ሰዓታቸው እንደ ኢትዮጵያውያት ወይዛዝር ወግና ልማድ የወይዛዝሮችን ባልትና ቀጭን ድርና ማግ መፍተልና ልዩ ልዩ የሆኑትን የቤት ውስጥ ባልትናዎች በሚገባ ጠንቅቀው በማወቃቸው የሴቶች ቁንጮ ወይም የሴቶች ራስ ለመባል በቅተዋል።
ባ፲፰፻፺፪ ዓ.ም. በሕግ ተድረው ሁለት ሴቶች ሁለት ወንዶች ወልደዋል። እነዚህም ወይዘሮ በላይነሽ ጃንጥራር አስፋው ፣ ጃንገብረ እግዚአብሔር ፣ ወይዘሮ ደስታ ናቸው።
ባ፲፱፻፫ ዓ.ም. ኅዳር ፭ ቀን ከደሴ ተነስተው ኅዳር ፳፫ ቀን አዲስ አበባ ደርሰው እንደ ቆዩ ፤ በዚሁ ዓመት በሰኔ ወር በዚያን ጊዜ “ደጃዝማች ተፈሪ” አሁን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለሆኑት ፤ ልጅ ኢያሱ ድረዋቸው የሠርጉም ሥነ-ሥርዓት ሐምሌ ፲፱ ቀን ፲፱፻፫ ዓ.ም. በሐረር ተከበረ።
፲፱፻፭ ዓመተ ምሕረት ጥር ፳፪ ቀን የመጀመሪያዋን ልዕልት ወለዱ።
የዓለም ስማቸውም በቅድም አያታቸው ስም ተናኘ ወርቅ ተብሎ ተሰየመ ፤ እኒህም ልዕልት በኮምቦልሻ ማርያም ጥምቀተ ክርስትና ሲቀበሉ ስመ ክርስትናቸው ፍቅርተ ማርያም ተብሎ ተሰየመ።
፲፱፻፰ ዓመተ ምሕረት ሐምሌ ፳ ቀን ፪ኛውን መስፍን ወንድ ልጅ ወለዱ። የዚህም መስፍን ስም አጠራር አስፋ ወሰን ተብሎ በግርማዊ አባታቸው ሲሰየም ጥምቀተ ክርስትናን በአደሬ ጢቆ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀብለው ስመ ክርስትናቸው አምኃ ሥላሴ ተብሎ ተሰየመ።
ባ፲፱፻፱ ዓ.ም. ሐምሌ ፲፰ ቀን ፫ኛዋን ልዕልት ወለዱ። የልዕልቲቱም ስመ ጥምቀት ሂሩተ ሥላሴ ተብሎ ሲሰየም ፤ የመጠሪያ ስማቸው ልዕልት ዘነበ ወርቅ ተብሎ ተሰየመ። ልዕልቲቱ ባ፲፱፻፳፭ ዓ.ም. መጋቢት ፲፭ ቀን ዘር ሳይተኩ ፤ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ባ፲፱፻፱ ዓመተ ምህረት መስከረም ፲፯ ቀን ልጅ ኢያሱ ከመንግሥቱ ሥራ በሕዝብ ድምፅ ሲወገዱ ፤ “ደጃዝማች ተፈሪ” ራስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ብልጫ ሲመረጡ ፤ ግርማዊት እቴጌም የልዕልትነት ማዕርግ ዕድል አገኙ።
፲፱፻፱ ዓ.ም. የካቲት ፬ ቀን ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በአባታቸው በአጼ ምኒልክ ዙፋን ሲቀመጡ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንም ወራሴ መንግሥት ሁነው የራስ ወርቅ አክሊል ሲቀዳጁ ግርማዊት እቴጌ የልዕልትነት የራስ ወርቅ ተቀዳጅተዋል።
በ፲፱፻፲፪ ዓመተ ምሕረት ጥቅምት ፪ ቀን አራተኛዋን ልዕልት ወለዱ። የሊህም ልዕልት ስመ ጥምቀት ወለተ ብርሃን ተብሎ ሲጠራ የመጠሪያ ስማቸው ልዕልት ፀሐይ ተባለ።
ባ፲፱፻፲፭ ዓመተ ምሕረት ጥቅምት ፪ ቀን አራተኛዋን ልዕልት ወለዱ። የሊህም ልዕልት ስመ ጥምቀት ወለተ ብርሃን ተብሎ ሲጠራ የመጠሪያ ስማቸው ልዕልት ፀሐይ ተባለ።
ባ፲፱፻፲፭ ዓመተ ምሕረት በወርኃ መጋቢት ግርማዊት እቴጌ ብፅዕትና ፈራሂተ እግዚአብሔር እንደ መሆናቸው መጠን ፤ መንፈስ ቅዱስ ስላነሣሣቸው ከቅዱሳት መጻሕፍት የሰሙትን ከቦታው ድረስ ሒዶ ለማየት አስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሁኖ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የተወለደበትንና ያደገበትን ፤ ተአምራት የሠራበትንና ዙሮ ያስተማረበትን ፤ ኋላም ለኛ ሲል በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የሞተበትንና የተቀበረበትን ፤ የተነሣበትን ቅዱስ ስፍራ ለመሳለምና እጅ ለመንሣት ብዙ አምኃና ለችግረኞች መርጃ ገንዘብ ይዘው ወደ ቅድስት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ በባቡር ፤ ከጅቡቲም በመርከብ ተጉዘው ኢየሩሳሌም ደርሰው ከላይ የተጠቀሱትን ቅዱሳት መካናት አንድ በአንድ ሲጎበኙ ሰንብተው ፤ እግረ መንገዳቸውን ወደ ምድረ ግብፅ ሒደው በዚያም ያሉትን የተቀደሱ ስፍራዎች አይተው ለየገዳማቱም ርዳታ ሰጥተው ተመልሰዋል።
ባ፲፱፻፲፮ ዓመተ ምሕረት ጥቅምት ፭ ቀን አምስተኛውን መስፍን ወለዱ። የመስፍኑም ስም በአያታቸው በራስ መኰንን ስም ዳግማዊ መኰንን ተብሎ ሲጠራ ፤ ስመ ጥምቀታቸውም አርአያ ዮሐንስ ተብሎ ተሰየመ።
ልዑል መኰንን መስፍነ ሐረር ግንቦት ፬ ቀን ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. አምስት ወንዶች መሳፍንት ትተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ባ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. መስከረም ፳፬ ቀን የኢትዮጵያ ሴቶች ልጆች ከወንዶች እኩል የዕውቀትና የሥልጣኔ ተካፋይ እንዲሆኑ በማሰብ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አጠገብ አዲስ ትምህርት ቤት አቋቋሙ ፤ ብዙዎች ሴቶች ልጆች በዚሁ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አድርገዋል።
ባ፲፱፻፳፫ ዓመተ ምሕረት ጥቅምት ፳፫ ቀን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ጭነው በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገሡ ጊዜ ፤ ግርማዊት እቴጌም በግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ “አንቺም እቴጌ እንድትሆኝ ፈቅደንልሻል” ብለው የእቴጌነት አክሊል አቀዳጁዋቸው።
ባ፲፱፻፳፫ ዓመተ ምሕረት የካቲት ፳ ቀን ፮ኛውን መስፍን ወለዱ። የሊህም መስፍን ስመ ጥምቀት በቅም አያታቸው በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አባ ዲና ስም ልዑል ሣህለ ሥላሴ ተብለው ተሰየሙ። ጥምቀት ክርስትናም በአዲስ አበባ መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሉ።
፲፱፻፳፮ ዓመተ ምሕረት መስከረም ፮ ቀን ለ፪ኛው ጊዜ ወደ ቅድስት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ሒደው ፤ ቅዱሳት መካናትን ሲጎበኙ ከቆዩ በኋላ ፤ በዮርዳኖስ ዳርቻ ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን መጠጊያና መጠለያ እንዲሆናቸው በርኅርኅትነታቸው ሰፊ አሳብና ችሮታ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ከግል ግምጃ ቤታቸው ወጭ አድርገው በስመ ሥላሴ ያሣነጹትን ቤተ ክርስቲያን መርቀው ለመነኰሳቱም ለገዳሙም መተዳደሪያ የሚሆን ሀብት ሰጡ።
፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ወራሪው ፋሽስት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ጦር ጭኖ ስለመጣ የኢትዮጵያን ሴቶች ሰብስበው ለዘማቹ ስንቅና ለቁስለኛው ቁስል ማሠሪያ የሕክምና መሣሪያዎች አዘጋጅቶ በመላክ እስከ መጨረሻው ድረስ ሲሠሩ ቆዩ።
ባ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ወራሪው ፋሽስት በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸመው ያጥቂነት ሥራ ለዓለም ሴቶች ማኅበር ጉባኤ አቤቱታቸውን ለመላው ዓለም አለመለከቱ።
💚💛❤️
የተናገሩት ቃል።
በዓለም ለሚገኙ ሴቶች ሁሉ ድምፃችንን ለማሰማት ዛሬ ማታ ምክንያት ስላገኘን እጅግ ደስ ብሎናል።
በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የአጥቂነት ሥራ ሊደረግበት በሚዘጋጅበት ጊዜ ፤ ሰላምንና ነፃነትን ለማፅናት የቆመው የዓለም ሴቶች ማኅበር ስለገለጠልን ፤ የጋለ የወዳጅነት አሳብ ጥልቅ የሆነ ምስጋናችንን ስናቀርብላቸው ደስ ይለናል።
አሁን የምንናገረውን ቃል ለሚያዳምጡ ሁሉ ትርጉሙ በቶሎ እንዲገባቸውና በመጠባበቅም ጊዜ እንዳይወስድባቸው አስበን ፤ እጅግ የተወደደች ልጃችን ፀሐይ በእንግሊዝ ቋንቋ ከተናገሩ በኋላ ልዕልት ፀሐይ ቀጥሎ ያለውን ቃል አነበቡ። “በሰውነታችን ላይ እጅግ የሚመዝነውና የሚከብደን ጦርነት እንዲደረግብን በታሰበበት ሰዓት አሁን በምንኖርበት በዚህ እጅግ ብርቱ በሆነውና በሚያሳዝነው ጊዜ ፤ በዓለም የሚገኙ ሴቶች ሁሉ በመላው ድምፃቸውን ማሰማትና አሳባቸውን መግለፅ ዋና የተገባቸው ነገር መሆኑን እናሳስባለን።
በዓለም ያሉት ሴቶች ምንም የሚኖሩበት አገር ልዩ ልዩ ቢሆን ፤ ነፋሱና አየሩም የተለዋወጠ ቢሆን ፤ ሴቶች ሁሉ ስለ ዓለም ሰላምና ፍቅር በተመሳሰለ ፈቃድ ፤ በአንድ ዓይነት ፈቃድ የተያያዙ ናቸው።
በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ጦርነት የሰውን ልጅ ከሚያስጨንቁ መከራዎች አንደኛ ብርቱ መከራ የሚያመጣ መሆኑ የተገለጠ ነው። በዓለም የሚገኙ ሴቶች ሁሉ ፤ በዘር በሃይማኖት በሀገር ልዩ ልዩ ቢሆኑ ፤ የኃይል ሥራ የሚፈጸምበት ጦርነት የሚያመጣው ፍሬ የሚያሠቅቃቸውና እጅግ የሚወዱዋቸውን ባሎቻቸውንም የሚጨርስባቸው ፤ ቤተሰባቸውንም የሚያጠፋባቸውና የሚበትንባቸው ስለሆነ ፤ ጦርነትን ይጠላሉ።
የኢጣሊያ ሴቶች መካንም የልጆችም እናት ቢሆኑ ፤ ማሠሪያ የሌለውና የማይመለስ ታላቅ መከራ የሚያመጣው የጦርነት አሳብ እንዲያስጨንቃቸው እናውቃለን። ስለዚህ በዓለም የሚገኙ ባል ያገቡ ፤ ያላገቡም ቢሆኑ ወላጆች ወይም መካኖች ቢሆኑ የሰው ደም በከንቱ እንዳይፈስ ለሸክም የሚከብድ መከራ በሰው ልጅ ላይ እንዳይደርስ ድምፃቸውን አስተባብረው መጮህና መጠየቅ ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ ምንም የኃይል ሥራ ለማድረግ አታስብም። ምኞቷ ሁሉ ሰላምን ለማግኘት ነው። ከብዙ ወራት በፊት ጀምሮ የተፈለገባትን ጥል ለማብረድ በማናቸውም ረገድ ቢሆን የተቻላትን አድርጋለችና ሕሊናዋ ንጹሕ ስለሆነ አይወቅሳትም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ በእውነተኛነት ሥራ ሠርተው ለመኖር የሚመጡትን የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ በወንድማማች አሳብ በደስታ ሲቀበል የኖረ ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕርዩ ከጥንት ጀምሮ ሲነገርለት የኖረ ታሪክ የሚመሰክርለት ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ጎረቤቷ የሆነው አንድ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላም ለመኖር በሚጣጣርበት ጊዜ የራሱን ጥቅም ብቻ በማሰብ ኢትዮጵያን በጦር ኃይል ለመያዝና ለመግዛት ተነሥቷል።
በኢትዮጵያ ወሰን ላይ ብዙ የጦር ሠራዊት አከማችቶ አገራችንን ለመውረር የኢትዮጵያን ሴቶች ባሎቻቸውን ልጆቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ለመግደል በሰላም እየሠራ ከእግዚአብሔር ጋር ተቃርቦ የሚኖረውን ሕዝባችንን አሠለጥናለሁ በማለት ምክንያት ፤ ቤተሰባችንን ለመበተን ፤ ንብረታችንን ለማጥፋት ይዘጋጃል።
ይህን በመሰለ መንገድ ከሚገኝ ኀዘንና የአገር መጥፋት ከሚያመጣ ሥልጣኔ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን እንለምናለን።
ስለዚህ የዓለም ሴቶች ያቆሙት የሰላም ማኅበር የሰውን ወገን ለመጠበቅና ታላቅ ኃላፊነት ያለባቸውና ለሕዝብ መሪ ለመሆን ክብር ያላቸው ሰዎች አሳብ ለሰላምና ወደሚስማማ መንገድ ለመምራት የሚያስፈልልገውን ሳያደርጉ ይቀራሉ ብለን አንጠራጠርም።
በዚህም በሚያስቸግር ሥራቸው እግዚአብሔር እንዲረዳቸው እንለምናለን። ሰላምን ለመጠበቅ በሚደክሙት ድካም እምነት ስላለን እስከ መጨረሻ እንዲገፉበት መልካም ፍሬም እንዲያፈራ ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን ጦርነት የግድ የተነሣ እንደሆነ እኛ ሴቶች ቁስለኞችን በማስታመም ጦርነት የሚያመጣባቸውን መከራ በተቻለ መጠን ለማቃለል የሚያሳዝነውን የተገባ ሥራችንን መፈፀም አለብን።
እኛም በዓለምም ያሉ ከእኛ ጋራ ሰላምን በመፈለግ አሳባቸውና ፈቃዳቸው አንድ የሆኑ ዛሬ በሐሳብ አንድ እንደሆነ በመከራችንም ጊዜ የሚረዱን ሴቶች ማግኘታችንን ስናስብ ያጽናናል። እነዚህም ሴቶች ቁስለኞችንና በክብር ለአገራቸው የሚሠውትንም አርበኞች ቤተ ዘመድ ለመርዳት እንዲያግዙን እናውቃለን።
በዓለም ያላችሁ ሴቶች ሁሉ በዓለም ላይ እውነተኛ ፍርድና ሰላም እንዲነግሥ የመንግሥት ሰዎች ሁሉ በሚሠሩት ሥራ በእግዚአብሔር መንፈስ እንዲመሩ በምናደርገው ጸሎት ተባባሪዎች እንድትሆኑ እንለምናለን።
ከ፲፱፻፳፰ ዓመተ ምሕረት እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ አገር በስደት በነበሩበት ጊዜያት ታቦተ መድኃኔ ዓለምን በሥዕል ቤት ስም አቋቁመው ፤ ሌትና ቀን በጸሎትና በሱባኤ ተወስነው ፤ ስለኢትዮጵያ መወረርና ስለሕዝብ በባዕድ አገዛዝ ቀንበር ሥር መውደቅ ሲያዝኑና ሲተክዙ ፤ ባንድ ወገን ደግሞ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የቅርብ ረዳትና አማካሪ በመሆን ፤ የነፃነት ብርሃን እስከታየበትና ዘመነ ሚጠት እስከሆነበት እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ድረስ ቆይተው ፤ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማየት በቅተዋል።
ባ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ኅዳር ፲፩ ቀን የኢትዮጵያን ሴቶች የሥራ ማኅበር ጎብኝተው ሥራው የሚስፋፋበትን ምክር ሰጡ።
ባ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ሐምሌ ፩ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ወንዶች ልጆች ልዩ ልዩ የእጅ ጥበብ ሥራዎች ሥጋጃ ምንጣፍና ሹራብ ይህን የመሳሰለውን የእጅ ጥበብ የሚማሩበትን ትምህርት ቤት መርቀው ከፈቱ።
ባ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ኮልፌ በሚገኘው ርስታቸው ላይ አባትና እናት ለሌላቸው በጠላት ጦር ጭካኔ ለቆሰሉት በጠቅላላው መጠጊያ ለሌላቸው ለድሆች ልጆች የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ቤት ከፈቱ። በዚህም ትምህርት ቤት ዕውራን ሳይቀሩ ማንበብና መጻፍ ይማሩበታል።
ባ፲፱፻፴፰ ዓመተ ምሕረት የካቲት ፳ ቀን የግርማዊት እቴጌ ትምህርት ቤት የሥራ ፍሬውን እያሳየ ብዙዎችን ሴቶች ልጆች በትምህርት በማሳደጉና ተማሪዎች እየበዙ በመሔዳቸው ትምህርት ቤቱ መጥበቡን በመረዳት ለ፫፻ ሴቶች ልጆች ማደሪያ የሚሆን አዲስ ሕንፃ እንዲሠራ መሠረቱን አኖሩ።
ባ፲፱፻፴፱ ዓ.ም. ሐምሌ ፲ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደባት ለቤተ ልሔም የእቴጌነትን ዘውዳቸውን እሰጣለሁ ሲሉ ፤ ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት መመለስ ባደረጉት ብፅአት መሠረት ፤ ነጻነት ተመልሶ ለዙፋን ቤታቸው ስለበቁ የእቴጌነትን ዘውዳቸውንና ሌላም ልዩ ልዩ መብዓ ላኩ።
ባ፲፱፻፴፱ ዓ.ም. በመናገሻ አውራጃ ግዛት ከአዲስ አበባ ከተማ በ፳፫ኛው ኪሎ ሜትር በሚገኘው ዓለም ገና ወረዳ “ሰበታ” በሚባለው ርስታቸው ላይ ጌቴሴማኒ ብለው ሰይመው ፤ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ከግል ግምጃ ቤታቸው በብዙ ሺ የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ አድርገው ዘመናዊ ሕንፃ አስጀመሩ።
ባ፲፱፻፵ ዓመተ ምሕረት መጋቢት ፳፭ ቀን በሰበታ ያስጀመሩት ጌቴሴማኒ የእመቤታችን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሞ ፤ ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ። ለካህናቱም መተዳደሪያ የሚሆን በአካባቢው የመኖሪያ ቦታና እርስት አከፋፍለው ሰጡ።
ባ፲፱፻፵፩ ዓ.ም. የልዕልት ዘነበ ወርቅ ትምህርት ቤት ያለበትን ቤትና ቦታ በርስትነት ለተማሪ ቤቱ ሰጡ።
ባ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ሐምሌ ፭ ቀን ፫፻፹ መጽሐፈ ቅዳሴ ኮልፌ ካላቸው ርስት ውስጥ ሰፊ ቦታና ቤቶች ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንና ለተማሪ ቤቱ መርጃ ሰጡ። በዚሁ ዓመተ ምሕረት የግሼን ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሳደሱ። እንዲሁም በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያወጣውን የስርጥ መንገድ አሠሩ። በዚሁ ዓመተ ምሕረት በጠላት ጊዜ ፈርሶ የነበረውን የቦሩ ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን እንደገና (ሃምሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ) ፶፮ ሺህ ፭፻ ብር አውጥተው አዲስ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል።
ባ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. በአዲስ ከተማ የቅዱስ ራጉኤልን ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የ፹፭ ሺህ የኢት.ብር “አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ብር” ከግል ገንዘባቸው አሠርተው ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑን መስከረም ፩ ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ.ም. አከበሩ።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. አንድ መቶ ለሚሆኑ እናትና አባት ለሌላቸው ድኆች ሕጻናት ማሳደጊያና መማሪያ የሚሆን በሁለት መቶ ሺህ ብር ከፍተኛ ሕንጻ አሠርተው ዛሬ መጠጊያ ያጡ ብዙዎች የድኆች ልጆች መማሪያና ማደጊያ ሆኗል።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. የደሴ መድኃኔ ዓለምን ቤተ ክርስቲያን የዙሪያውን እድሞ አጥር በደንብ አሠርተዋል።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. የሚጣቅ አማኑኤልን ቤተ ክርስቲያን የቀድሞውን ሥራ በማሻሻል ከማሠራታቸውም በላይ ወደ ጸበሉ ከየሀገሩ የሚመጡት በሽተኞች የሚያርፉበት በማጣት የሚደርሰውን ችግር ለማቃለል አሥራ አራት ክፍል ቤት አሠርተው ጠበልተኞቹ በቁርና በሐሩር ከመጠበስ ድነው እየተፈወሱ የሚሔዱ ብዙዎች ናቸው።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. በትግሬ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ቀረጻ ማርያም የተባለችው ገዳም የተሠራችው ከታላቅ ጋራ ላይ ስለሆነ በገዳሙ ውስጥ በሚኖሩት መነኮሳት የሚደርሰውን ችግር ለማስወገድ ታላቅ የውሀ ማጠራቀሚያ በገንዘባቸው አሠሩ።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. በትግሬ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ደብረ አባይ በተባለው ገዳም የሚኖሩ መነኰሳት የሚረዱበት ለማኅበሩ መርጃ የሚሆን አንድ የእህል መኪና ወፍጮ በገንዘባቸው ገዝተው ሰጡ።
ባ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. ዓለም ገና ላሠሯት ለጌቴ ሴማኒ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መርጃ አዲስ አበባ ከተማ አንድ ቤት በ፳፭ ሺህ ብር አሳንጸው ከነቦታው ሲሰጡ ደግሞ በ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. በ፳፭ ሺህ ብር አሠርተው ለመርጃ እንዲሆን ሰጥተዋል።
ባ፲፱፻፶ ዓ.ም. በሜጫና በጅባት አውራጃ ሀገረ ሕይወት አጠገብ የአዋሮ ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ አቅድ አሠሩ።
ባ፲፱፻፶ ዓ.ም. ደሴ ከተማ ለሁለት መቶ ወጣቶች መማሪያ የሚሆን አንድ ታላቅ የጅ ጥበብ ትምህርት ቤት በ፩፻፰ ሺህ ብር አሠርተው ለሥራ ውሏል።
ባ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. ለመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን መርጃ ቀድሞ ቄራ ከነበረው ከግርማዊት እቴጌ ቦታ ውስጥ በሐያ አምስት ሺህ ብር የተሠራ አንድ ቤት በርስትነት ሰጡ።
ባ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. ኢየሩሳሌም በሔዱ ጊዜ ዮርዳኖስ ድረስ በሙሉ ጎብኝተው በኢየሩሳሌም ላሉት ገዳማትና መነኮሳት ብዙ የገንዘብ ችሮታ አደረጉ። በዚሁ ዓመተ ምሕረት ኢየሩሳሌም ዮርዳኖስ ላሠሩት ቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ እንዲሆን አዲስ አበባ በሙኒዮ መንገድ ላይ በ፳፻ ሺህ ብር ያሠሩትን ቤትና ቦታ በርስትነት ሰጥተዋል።
ባ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል አጠገብ ለሕዝብ በነጻ መታከሚያ ክሊኒክ ሆስፒታል አሠርተዋል።
ባ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. አሥመራ ለማኅበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት ለነጻነት መድኃኔ ዓለም ለማኅበሩና ለቤተ ክርስቲያኑ መርጃ የሚሆን ካባራቶሉና ኩባንያ ጥጥ ፋብሪካ አክሲዮን ገዝተው ሰጥተዋል።
ግርማዊት እቴጌ መነን የሴቶች ሥልጣኔና ዕድገት የሚስፋፋበትን መንገድ አዘውትረው ፤ የብዙ ድርጅትና የማያቋርጥ ርዳታ ባለቤት እንደመሆናቸው መጠን ፤ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ በልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ሴቶች የበጎ ሥራ አገልግሎት ማኅበር ፕሬዚዳንት ንግግር ከፋችነት ፤ በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ተካፋይ በመሆን ለመጡት የአፍሪካ ሴቶች የጥናት ጉባኤ ስብሰባ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከተውን የማበረታቻ መልእክት ለጉባኤው ልከዋል።
የግርማዊት እቴጌ መነን መልእክት።
የዓለም ሕዝብ እውነተኛ የሆነ መግባባትና ወዳጅነት እንዲገኝ ለማድረግ እንዳሁኑ ዘመን ባለማቋረጥ የጣረበት ጊዜ አልነበረም። ፈጣን የሆነ መለዋወጥ በሚያደርግበት ባሁኑ ጊዜ ፤ እናቶች ለጎረቤቶቻቸውና በጠቅላላው ለሰው ዘር ሙሉ የሆነና የጋለ ፍቅር በማሳየት ፤ እንደዚሁም ቤታቸውን በመውደድ የሚዋልለውን ዓለም ለማረጋጋት የሚችሉት እነሱ ናቸው። መልካም የሆኑ የዓለም መሪዎች እንዲገኙ ለማድረግ ለልጆች የጋለ ፍቅር በማሳየት በሚገባ በማሰብ በየበኩላችን እንርዳ። ይህን የመሰለው መንፈስ ለአፍሪካና ለመላውም ዓለም የወደፊት ዕድገት መሪ መሆን አለበት ፤ መጭው ትውልድ የሚጠቀምበትን ፕላን ለማዘጋጀትና አስፈላጊውን መምሪያም ለማግኘት በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የሚገጥመን ዕድል ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይሄዳል።
በመላው ታሪካችን ውስጥ ሳያቋርጥ የነጻነት ነፋስ በኃይል ሲነፍስበት በኖረው የንግሥተ ሳባ አገር ወደ ሆነው አገራችን እንኳን ደህና መጣችሁ ስንላችሁ ደስታ ይሰማናል።
ከመነን!
ባ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. ከግርማዊት እቴጌ መስክ ከንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስ ቦታ አዋሳኝ ቀድሞ በጭሰኝነት ለሠፈሩት ለአምስት መቶ ሰላሳ ሶስት ሰዎች ሶስት መቶ ካሪ ሜትር በርስትነት ከመስጠታቸው በላይ ፤ የተረፈውንም ቦታ ለሌላው ደጅ ጠኝ ከፍለው ሰጥተዋል።
በዚሁ ዓመተ ምሕረት ከቡና ቦርድ አቅራቢያ የሚገኘውን ርስታቸውን እንደዚሁ ቦታ ለሌላቸው ሰዎች አከፋፍለዋል።
ግርማዊት እቴጌ መነን ከርኅርኅትነታቸው የተነሣ ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ያለ የእናትነት ሥራቸውን ፈጽመውለታል። ይኸውም በወህኒ ቤት ለሚገኙ እሥረኞች ሥላሴና መድኃኔዓለም በሚውሉባቸው ቀናት በየወሩ ለየአንዳንዱ እሥረኛ በቂ የሆነ የምሣ ግብር ይደረግላቸው ነበር። እንደዚሁም ለነዚሁ እሥረኞች በየዓመቱ ብዙ ሰንጋ እየታረደ ሥጋው ከነ ማጣፈጫው ጭምር እየተሰጣቸው ይመገቡ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. በጥር ወር አሥራ ስምንት ሰንጋ ታርዶላቸው ተሰጥቷቸዋል። ግርማዊት እቴጌ መነን ይህን ሲያደርጉ ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ነው።
ከዚህም በቀር ግርማዊት እቴጌ የርኁባን ምግብ ፤ የጽሙን መጠጥ ፤ የርኡቃን ልብስ ፤ የሽማግሌዎች ጠዋሪ እንደመሆናቸው መጠን ፤ በግርማዊነታቸው ቦታ ላይ ቤት ተሠርቶ ከሰላሳ የሚበልጡ ድኩማንና እርኁባን በየቀኑ የምሳ ድርጎ ያገኙ ነበር። እንደዚሁም ከአምስት መቶና ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሽማግሌዎች የገንዘብና የእህል ድርጎ እየተሰጣቸው የሚጦሩ ነበሩ።
ግርማዊት እቴጌ መነን የመጻሕፍት ቅዱሳትን ቃል በመፈጸም በቤተ ክርስቲያን በኩል የሰጡት ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት እንዲያውም በጣም የሌሊት ሰዓታት የሚቆምበት ፤ ጸሎተ ቅዳሴ የሚደርስበት መብራት ችግር በሆነበት ዓመታት ብዙ የገንዘብ ወጭ እያደረጉ ፤ በመላው በኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሰጥተዋል። ግርማዊት እቴጌ መነን በአልባሳት በኩል ያለውን ችግር ለማቃለል ፤ በተለይ ሰባት ሰዎች ልብሰ ተክህኖ የሚሰፋ ቀጥረው ፤ ተፈላጊውን የጨርቅ ዓይነት ከውጭ ሀገር በማስመጣት ፤ ለብዙዎች ቤተ ክርስቲያን አልባሳትን ሰጥተዋል። ከዚህም ሌላ ለየገዳማቱ የሰጡት ምጽዋትና ሊሠሩ ተጀምረው ያስፈጸሟቸው አብያተ ክርስቲያናት እጅግ የበዙ ናቸው።
የካቲት ፲፱፻፶፬ ዓ.ም.
ሞዓ አንበሳ
አሸናፊው የይሁዳ አንበሳ
════༺❀༻༺❀༻════╗
ዕዝራ ሱቱኤል
የጥናትና ምርምር ማዕከል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top