በአክሊሉ ማስታወሻ ላይ ስለዚያ ቀውጢ ጊዜ የሠፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል/ Aklilu Habtwold Journal-The late Ethiopia Prime Minister

Thomas Wold
የናዚ ጀርመን ጦር የፈረንሣይን የመከላከያ ኃይል ሰባብሮ ወደ ፓሪስ መገስገሱ ሲታወቅ ጠቅላላው የፈረንሣይ መንግሥት ቦርዶ (Bordeaux) ወደተባለው የደቡብ-ምዕራብ ፈረንሣይ ከተማ ተሰደደ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ ፈረንሣውያን ወደ ቦርዶ አቅጣጫ በመሸሽ ላይ ነበሩ፡፡ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ የነበረው ወጣቱ አክሊሉ ሀብተወልድ ኤምባሲውን ዘግቶ በፍጥነት ፓሪስን መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ ወራሪው የናዚ ሠራዊት ከደረሰበት እጁን ይዞ ለፋሺስት ኢጣሊያ እንደሚሰጠው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአክሊሉ ማስታወሻ ላይ ስለዚያ ቀውጢ ጊዜ የሠፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡፡
‹‹ፓሪስን ጀርመኖች እንዲሁም ጣልያኖች ሳይዙት ከሶስት ባልንጀሮቼ (መከብብ፣ ሥዩምና ሉቃስ) ጋር በቢስክሌት ከፓሪስ ወጥተን ወደ ቦርዶ ተጓዝን፡፡ ቢስክሌቱን ለመግዛት የቻልኩት በማድሟዜል ኮሌት (በስተኋላ የትዳር አጋራቸው የነበሩት የፈረንሣይ ወይዘሮ) እርዳታ ነው፡፡ ከነመክብብ ጋር ተጠፋፍተን ቦርዶ ድረስ አብረን ለመድረስ የቻልነው እኔና ሉቃስ ብቻ ነበርን፡፡ በመንገድም ብዙ ውጣውረድ ደርሶብን፤ እንዲያውም የፈረንሣይ ወታደሮች በጦር ቀጠና ውስጥ ሌሊት መብራት አብርታችኋል በማለት እንድንገደል አዝዘው ሳለ ሳይገድሉን በፊት ጀርመኖች ስለደረሱ ከሞት ተረፍን፡፡
‹‹ወደ ቦርዶ የሄድኩት እንግሊዞችን የሚያሳፍር አንድ መርከብ አለ ስለተባለ በዚያ ተሳፍሬ ወደ እንግሊዝ አገር ለመጓዝና ከጃንሆይ ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ጧት ስንደርስ መርከቡ ለካስ ማታ ሄዶ ኖሯል፡፡ በመጨረሻው መርከብ አንድ የፈረንሣይ መንግሥት ዲፕሎማት የሚሄድ መሆኑን ስሰማ ወደ እንግሊዝ አገር እንድሄድ የይለፍ ወረቀትና ማንኛውንም እርዳታ እንዲያደርግ ብጠይቀው፤ ‹‹እኛ አሁን ተሸንፈናል፤ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ደግሞ በአደረግነው የ‹‹አርሚስቲስ›› ውል መሠረት የጣልያንና የጀርመን ጠላት የሆነ አገር ዜጋ ፈረንሣይን ለቅቆ እንዳይሄድ ውል ገብተናል፡፡ ከዚህ መሄድ አትችልም›› አለኝ፡፡
‹‹የፈረንሣይ አዲስ መንግሥት ከፒተ ወደ ቪሽ እንደሄደ እኔም በድንኳን ውስጥ ቆይቼ ወደዚያው ተከትዬ ሄድኩ፡፡ እዚያም የፈረንሣይ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ላቫል ስለነበረ እንደገና ከፈረንሣይ ለመውጣት እንዲፈቀድልኝ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እሱ የነሂትለር ደጋፊ ስለነበረ፤ ‹‹እንዲያውም አሁን ፈረንሣይ ኢትዮጵያን ስለማታውቅ ፓስፖርትህ መወሰድ አለበት!›› ብሎ ፓስፖርቴን ነጥቆ፤ ማርሴይ ውስጥ ‹‹ሬዚዶንሴ ፊክሴ›› (ቋሚ ነዋሪ) አድርጎ ከዚያ እንዳልነቃነቅ አዘዘ፡፡
‹‹ቢሆንም እኔ ሌላ ፓስፖርት አዘጋጅቼ በድብቅ ቪሽ ከተማ እየመጣሁ ከውጪ አገር አምባሳደሮች ጋር ንግግር እያደረግሁ፤ ከፈረንሣይ ለመውጣት እጣጣር ነበር፡፡ እቅዴ ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ሌላ አገር ቪዛ አግኝቼ ከፈረንሣይ ለመውጣትና ወደ እንግሊዝ አገር አቅንቼ ከጃንሆይ ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ በብዙ ድካም የአሜሪካንና የሜክሲኮን ቪዛ ያገኘሁ ቢሆንም በፓስፖርቴ የተነሳ ከፈረንሣይ ለመውጣት አልቻልኩም ነበር፡፡
‹‹ከብዙ ውጣውረድና ችግር በኋላ ማርሴይ የነበረው የኮሎምቢያ ቆንሲል ሁኔታዬ አሳዝኖት የኮሎምቢያ ፓስፖርት ሰጠኝ፡፡ በዚህ ፓስፖርት ዜግነቴ ኮሎምቢያዊ ሆኖ ስሜም ቶማስ ወልድ ተብሎ ነበር፡፡
‹‹በዚህ ፓስፖርት ረዳትነት ከማርሴይ አገረ ገዢ ጋር በሚሥጥር ተነጋግሬ በብዙ ውጣውረድ ፈረንሣይን ለቅቄ ለመውጣት ቻልኩ፡፡ ከፈረንሣይ ከመነሳቴ በፊት ማርሴይ ለነበረው የአሜሪካ አምባሳደር የራሴን ትክክለኛ ፓስፖርት ሊዝቦን (የፖርቱጋል ዋና ከተማ) ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲልክልኝ ሰጥቼው ሄድኩ፡፡ የሄድኩትም በስፔን ወደ ፖርቱጋል ነበር፡፡ ፖርቱጋል የዚያን ጊዜ ‹‹ኒውትራል›› ገለልተኛና የእንግሊዝም ወዳጅ ስለነበረ የምፈልገውን እርዳታ ያለችግር ለማግኘት ቻልኩ፡፡ ሊዝቦን ስደርስ ወዲያውኑ ከማርሴይ የተላከልኝን ፓስፖርት ከአሜሪካ ኤምባሲ ተቀበልኩ፡፡
‹‹ፖርቱጋል፤ ሊዝቦን የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ሄጄ ፈረንሣይ ውስጥ መውጫ አጥተው የቀሩትን ወንድሞቼን (መክብብና መኮንን) እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለማስወጣት እርዳታቸውን ጠየቅሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ነጻነት ተመልሶ ጃንሆይም አዲስ አበባ ገብተው ስለነበረ፤ አምባሳደሩ ወደ አዲስ አበባ ቴሌግራም ካደረገ በኋላ ሊረዳኝ ፈቃደኛ መሆኑን ነገረኝ፡፡
‹‹ፈረንሣይ ከቀሩት ኢትዮጵያውያን ጋር እየተጻጻፍኩ እነሱም ለመውጣት የሚችሉበትን ከየኤምባሲዎቹ ጋር ተነጋግሬ እንዲወጡ አደረግሁ፡፡ መርከብ እንደተገኘ ከሁለት ወር በኋላ በደቡብ አፍሪካ ዞሬ ወደ ሞምባሳ (ኬንያ) ለመድረስ ቻልኩ፡፡ አዲስ አበባ የደረስኩት እ.አ.አ በ1941 ዓ.ም መጨረሻ ላይ (ታህሳስ ወይም ጥር 1934 ዓ.ም) ነበር››
May be an image of text that says 'REPÚBLICA DE PASAPORTE CONSULADO DE COLOMBIA, 33 Rue Saint-Jaoques, MARSELLA, FRANCIA. CÓNSUL DE COLOMBIA MARSELLA CERTIFICA que el señor THOMAS eaлиTa Andrés (Intendenola Andrés Providencia) Republi edad oomeroiante soltero, cuya fotografia aparece CIUDADAN COLOMBIAN Expedido Marsella alos trei- mes de mil novecientos cuarenta. 30 AOOT 1940 asul de Colonbia. DATOS DEL TITULAR BIODATA APELLIDOS: Wold NOMBRES: Thomas NACIONALIDAD: Colombiana FECHA DE NACIMIENTO: 10 ENE 1912 LUGAR DE NACIMIENTO: San Andrés M PROFESIÓN: STADO CIVIL: ThrAR Comerciante Soltero NOTA:- titular DODA- Poo Οά repatria opor 11aho elco- RACItO netruccio reclbidas miestro Gobiorno. hlala Cónsul de Colombia AASELLA A 345678'
©akliluhaptewold/facebook.com

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top