አክሊሉ ሀብተወልድ ከሁለት ወንድሞቻቸው (አካለወርቅና መክብብ) ጋር አዲስ አበባ ውስጥ የፈረንጅ ትምህርትን አሀዱ ብለው የጀመሩት፤ በ1911 ዓ.ም አጋማሽ ላይ፤ በአሊያንስ ፍራንሴዝ ት/ቤት ውስጥ የፈረንሣዊኛ ቋንቋና ሒሰብ በማጥናት ነበር፡፡ ከስድስት ወር በኋላ መስከረም 20 ቀን 1912 ዓ.ም ሶስቱ ሀብተወልዶች፣ በዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት የሚሰጠውን መደበኛ ትምህርት መከታተል ጀመሩ፡፡ እነዚህ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ቀደም ብለው የፈረንሣዊኛ ቋንቋና ሒሳብ በማጥናታቸው ከሌሎች ተማሪዎች በመምሕራኑ ዘንድ የተሻለ ግምት የተሰጣቸው ነበሩ፡፡ በዚህ ት/ቤት ውስጥ በቆዩበት በ7 ዓመታት ውስጥም በትምህርት አቀባበላቸውም ሆነ በጠባያቸው ምስጉኖች ነበሩ፡፡
እንግዲህ በዚያን ዘመን የፈረንጅ ትምህርትን ከአንደኛ ደረጃ በላይ ለማስተማር የሚችል ት/ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ አጥጋቢ ችሎታ ያላቸውን ልጆች እየመረጡ አልጋ ወራሽ ልዑል ተፈሪ መኮንን ወደ ውጪ አገር እየላኩ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ተምሕርት እንዲማሩ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህን የውጪ አገር የትምህርት ዕድል ሶስቱ ሀብተወልዶች ለማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ ግን የቤተሰባቸውን ፈቃድ ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ በዘመኑ የነበረው የቤተሰብ አስተሳሰብ ልጆቹ ከአገራቸው ርቀው ሲሄዱ ሃይማኖታቸውን ይቀይራሉ የሚለው ዋንኛው ፍርሃት ስለነበረ ነው፡፡
አሳዳጊያቸው አቶ መኮንን ሀብተወልድ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ሹመት የተሰጣቸውና የዘመናዊ አስተዳደር ደጋፊ እንደመሆናቸው የወንድሞቻቸውን ወደ ውጪ አገር ተጉዞ መማር ከልባቸው የሚደግፉት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን አሳብ ለእናታቸው ለእማሆይ ያደግድጉ አስረድቶ ማሳመኑ ቀላል ስላልሆነላቸው የእናታቸውን የንስሐ አባት በአማላጅነት መላክ አስፈልጎ ነበር፡፡
ንስሐ አባታቸው መምሬ ገ/ዮሐንስ በውጪ አገር ተጉዞ አዲሱን የፈረንጅ ትምህርት የመቅሰምን አስፈላጊነት ለእማሆይ ያደግድጉ ሲያስረዱ ‹‹…አቶ መኮንን እንደነገረኝ እነዚህ ልጆቻችን ለከፍተኛ ዕውቀት በአልጋወራሽ ትዕዛዝ የሚላኩበት እስክንድርያ [Egypt, Alexanderia] የተባለው አገር፤ ከብዙ ዘመናት በፊት፤ እነአባ ፍሬምናጦስ፣ እነአባ ማትያስ፣ የተማሩበት ስለሆነ በእውነቱ ልጆቻችን ላጋጠማቸው ይህን የመሰለ ትልቅ ዕድል፤ ከዚህ የበለጠ ደስታ ሊኖረን አይችልም …›› በማለት ተናገሩ፡፡
ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ብልህነትና አስተዋይነት ያላቸው መነኩሲት የሰጡት መልስ፤ የተነገራቸውን ሁሉ ከልባቸው አምነው የተቀበሉት አይመስልም፡፡ እማሆይ ያደግድጉ ሲመልሱ ‹‹ …ጌታችን አልጋ ወራሽ በዚያ ሁሉ ከባድ ሥራቸው ላይ ለእኔ ለአልባሌዋ ልጆች በማሰብ፤ ወደ ውጪ አገር ሄደው የፈረንጅ ትምህርት እንዲማሩ ያዘዙት እሳቸው ከሆኑ፤ እኔ ምን እጨምርበታለሁ? …እግዚአብሔር በደህና ጠብቆ በሰላም ወስዶ እንዲመልሳቸው ከመጸለይ በስተቀር በእኔ በኩል የሚደረግ ነገር የለም፡፡ አባቴ አሁን ሲናገሩ፤ መኮንን ያስጠናዎትን አስታውሰው፤ ልጆቻችን የሚሄዱት ታላላቆቹ ጻድቃኖች ወደተማሩበት አገር ስለሆነ፤ መደሰት አለብን ብለዋል፡፡ እንደእኔ እንደ መሐይሟ አሳብ ከሆነ ደስታ በጅምሩ ከሚሆን፤ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ሲታይ ይሻላል›› ካሉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ልጆቻቸው መለስ አድርገው፤ ‹‹…እናንተ ልጆች! ይኸው የፈረንጅ ትምሕርት ለመማር ወደ ፈረንጅ አገር እንድትሄዱ ታዛችኋል ተብሏል፡፡ ፈረንጅ አገር ሄዳችሁ ምን ተምራችሁ፤ ምን መስላችሁ እንደምትመለሱ ባላውቅም፤ በምትኖሩበት አገር ሁሉ የሃይማኖታችሁን ጉዳይ በቅጡ እንድታስቡበት አጥብቄ አደራ እላችኋለሁ፡፡ ወንድማችሁ መኮንን በቶሎ እንደምትሄዱ ሲነግረኝ፤ ትምሕርታችሁ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያቆያችሁ አልገለጠልኝም፡፡ ስትመለሱ፤ ምናልባት ልታገኙኝ ወይም ላታገኙኝ ትችላላችሁ፡፡ ትልቁ ቁምነገር የኔ መኖርና አለመኖር አይደለም፡፡ እንደተመለሳችሁ፤ ለደጉና ለታዋቂው አባታችሁ ለአለቃ ሀብተወልድ ስም ማስጠሪያና መታሰቢያ ሆኖ የሚኖር፤ በደብረ ኃይል ራጉኤል አንድ ነገር እንድታቆሙላቸው እለምናችኋለሁ፡፡ ትንንሾች ልጆች በነበራችሁበት ጊዜ እንደምጨቀጭቃችሁ፤ የራጉኤል ደብራችንን እንደአባታችሁ አገልግሉ አልላችሁም፡፡ ዛሬ ጊዜው ተለውጧል፡፡ እናንተም ተለውጣችኋል፡፡ ግን፤ አንድ መታሰቢያ የሚሆን ቋሚ ነገር መሥራት አያቅታችሁም እላለሁ…›› በሚል ቃል እማሆይ ያደግድጉ ልጆቻቸውን አሰናበቷቸው፡፡
